በሚስጥር የተላከ
(አንቺ/እሷ)

ቡች ምንድን ነው?
በተለምዶ የሌዝቢያን ባህል ‘ቡች’ የሚለው ቃል የሚያመለክተው በተፈጥሮ የሴት ተክለሰውነት ይዛ የተወለደች ሴት ሆና ሴት አፍቃሪ የሆነች እና ባህሪዋ በተለምዶ ‘ወንዳ ወንድ’ የምትባለውን ሴት የሚገልጽ ነው። ብዙ ጊዜ ቡችዎች በዙሪያቸው፣ ስለ ጾታ ሚናዎች፣ በባህሎች እና በታሪክ በማህበረሰብ ውስጥ የነበሩ እሳቤዎችን የሚፈታተኑ ሆነው ብዙ ጊዜ ይታያሉ። ቡች ሌሎች ብዙ ነገሮችንም ሊያመለክት ይችላል። ዛሬ እንደ ሲስ ሌዝቢያን ሴት ወይም ሴታሴት ሴት ሌዝቢያን፤ ቡች መሆን በእኔ እይታ ምን ማለት እንደሆነ ለመናገር ልሞክር።
ቡች መሆን ልብስ እና አቀራረብ ብቻ አይደለም። ቡች መሆን ከልብስ እና አቀራረብ በዘለለ የአኗኗር ዘይቤ እና በዘልማድ “የወንድ” ሚናዎችን እና ስራዎችን ወይም በዘመናቸው እንደ “የወንድ ተግባር ብቻ” ይታሰቡ የነበሩ ተግባሮችን መከወንንም ሊጭምር ይችላል። ቡች አቀራረብ እንዳላት ሴት፣ በማህበረሰቡ ውስጥ ያለው መርዛማ የወንድነት ባህሪ (Toxic masculinity) የተሳሳተ እና ከማንነቴ አካሄዴን የሚያስት መረጃ ነበር። እኔ የበላይ መሆን እንዳለብኝ፣ ጠንካራ መሆን እንዳለብኝ፣ የተጠበቅኩ መሆን እንዳለብኝ፣ ጨዋ እና ድምጸ-ከል መሆን እንዳለብኝ፣ በዙሪያዬ ካሉ የወንድ ምስሎች የተወሰዱ ባህሪያትን ማንጸባረቅ እንዳለብኝ እንዳምን አድርጎኛል።
ወንድነትን በተመለከተ ጎጂ የሆነ ግንዛቤ ነበረኝ፣ ይህም የሴትነት ማንኛውንም ነገር ከድክመት፣ ከደካማነት እና ታዛዥ ከመሆን ጋር ስላያያዝኩት እንዳልቀበል አድርጎኛል።
ቡችነቴ እራሴን መሆን ብቻ ሳይሆን አልፋ ወንድ መሆንን እና አንድ ወንድ ምን መምሰል እንዳለበትም ጭምር የሚያስረዱ ጠንካራ የሆኑ ጎጂ አመለካከቶችን መቀበል ነበር። እኔ እንደዚያ አይነት ሴትም ባልሆንም ራሴን ወደ አሉታዊ ሃሳቦች እና ለማንም የማይጠቅም ባህል ለመቅረጽ እየሞከርኩ ነበር።
ቡች መሆን በዘልማድ ከሚጠበቀው ነገር ጋር መጣጣም ሳይሆን እነሱን ታግሎ በማሸነፍ እራስን መሆን መሆኑን እያወቅኩ ነው።
ቡችነት፣ ለእኔ፣ ወንድ ከመሆን ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። በእውነቱ ሴት መሆን፣ እንደ ሴት ስለመለየት አንድ አገላልጽ ነው። ይህ በእውነት እኔነቴን የሚያስተጋባ አቀራረብ ነው።
በተጨማሪ፣ የቡች ማንነቶችን ማድነቅ፣ መወከል እና ማክበር ይበልጥ አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ። እንደማንኛውም የተለመደውን ሃሳብ እንደሚፈታተን ማንነት ሁሉ፣ ቡች ሴቶች እራሳቸውን በመሆናቸው ብዙ ጊዜ ተቃራኒ ወይም አሉታዊ ምላሽ ሊያገኙ ይችላሉ።
ይህም በቃል በየመንገዱ “ከቤ” እና “ጎረምሳው” ከመባል ጀምሮ እስከ አካላዊ ጥቃት፣ በተደጋጋሚ እና በግልፅ “ወንድ” ከማለት፣ “ከሴት ቦታዎች” እንድንወጣ እስከ መንገር ድረስ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሁሉ ነገሮች በእኔ ላይ ደርሰዋል፤ ለብዙ ሌሎች እኔን መሰል ሴቶች የማይታወቁ ተሞክሮዎች እንደማይሆኑ እርግጠኛ ነኝ።
ዛሬ ለኔ ቡችነት ማለት ጥንካሬ ነው።
ዛሬ ቡችነት ለእኔ ጥንካሬ ማለት ነው። ላመንበት ነገር መቆም። ድጋፋችን የሚያስፈልጋቸው እርዳታችንን ሲፈልጉ ቀድሞ መገኘት እና እርስበእርስ መጠባበቅ ማለት ነው። ይህ ማለት መቼ ድምጸ ታቅቦ መስጠት፣ መቼ መደገፍ፣ መቼ መቃወም፣ መቼ መከታተል፣ መቼ መንከባከብ፣ መቼ መማር፣ መቼ ማደግ፣ መቼ ስሜታዊ መሆን፣ መቼ ተጋላጭ መሆን እና መቼ መሳቅ እንዳለብን ማወቅ መቻል ማለት ነው።
እነዚህ ሁሉ ነገሮች እኔ በማውቃቸውና በጣም ጠንካራ በሆኑ ሴቶች ባህሪያት ውስጥ የተካተቱ ማንነቶች ናቸው፣ ቡች ሆኑም ወይም ሌላ ይሄ በቀጥታ ከሴትነታቸው ጋር የተያያዘ ነው። ለኔ ቡች ዝም ብሎ “ተባዕታይ” ማለት አይደለም፣ ውስብስብና ጉልበት የሚሰጥ የማንነት መግለጫ ነው። ከፊት ለፊቴ ቡችነታቸውን ለብሰው በኩራት ላሉት እና ጥሩ አርዓያ ለሆኑ ሴቶች ምስጋና ይግባና ዛሬ ቡችነቴ በኩራት የምለብሰው ባጄ ነው።

